የመንግስት ተቋማት ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያችላቸውን የሪፎርም ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ።
20-04-2026 09:04am የመንግስት ተቋማት ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያችላቸውን የሪፎርም ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ፣ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት አሰጣጥና የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለውን የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ካሳ አበባው ገልፀዋል።
እየተከናወነ የሚገኘው የመንግስት አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ ካርታ ያለው፣የህግ ማዕቀፍ ያለውና ስትራቴጅዎችን ተከትሎ የሚፈፀም መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ የሪፎርሙ አካል መሆኑንም የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ አዲሱ የመንግስት ተቋማት ሪፎርም ብቃት ያላቸው ሰራተኞችን ለማፍራት አጋዥ ነው ።
አዲስ የወጣው አዋጅ የመንግስት ሰራተኛውን ጥቅም ያካተተ ነው ይህንንም አዋጅ በሰፊው ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
ብቃት ያላቸው ሰራተኞችን ለማብቃት የብቃት ፈተና የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገራችን ሪፎርም ተቀርፆ ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ስራዎች እየተተገበሩ ነው ያሉት ሌላዋ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ምትኩ
ከተያዙት ዋና ተግባራት አንዱ ዲጅታል የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ሲሆን በተደራጀ መንገድ በርካታ ተቋሞችን በአንድ ማእከል አገልግሎት እንዲሠጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደ ክልሉ በ3ቱ ማእከል የሞሰብ አንድ ማእከል አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ሲሆን 40 የፌደራልና የክልል ተቋማት ከ202 በላይ አገልግሎቶች ቀርበዋል።
በእነዚህ ማእከልም ከ51ሺ በላይ ተገልጋይ ተገልግለውበታል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ማህበረሰቡም በመሶብ አገልግልት ከ95%በላይ እርካታን ያመጣ ሲሆን ይህንን አገልግሎት ለማስፋት በ3ዙር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለተኛ ዙርም 5 ሪጅኦ ፖሊታን ከተሞች የሞሰብ አንድ ማእከል አገልግሎት በቅርብ ጊዜ የሚጀምሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በ3ኛ ዙርም 25 የዞኖች ዋና ከተሞች እና ከተማ አስተዳደር ላይ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጣችንን በመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት በመስጠት እያዘመን ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ሲቪልሰርቪስ እና የሠውሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠለሞን በዛብህ 14 የፌደራልና የከተማ አስተዳደር ተቋማትን በማስገባት 74 የአገልግሎት አይነቶችን በአንድ ማእከል ድጅታላይዝ አገልግሎት እየተሠጠ መሆኑን ገልፀዋል።
እሰከአሁን ድረስም በመሶብ አንድ ማእከል ከ7ሺህ 2መቶ በላይ ተገልጋይ ተጠቃሚ ሲሆኑ በአገልግሎቱ የተሻለ እርካታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በሁለት ቀናት የስልጠና ቆይታ የግማሽ ዓመቱን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መገምገም፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተመለከተና በአዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ላይ ውይይት የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል።
በውይይቱም የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የዋግህምራ፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ የኦሮሞ ብሂረሰብ አስተዳደር፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የዘርፉ የስራ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት ፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የቴክኒክ ኮሜቴ አባላት ተሳታፊ ናቸው ።

